"ሀገራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ባዳረገ መልኩ ኢኮኖሚን መምራት ይገባል" - ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ (የገቢዎች ሚኒስትር) መጋቢት 22/2018 ዓ.ም የገቢዎች እና የፍትህ ሚኒስቴሮች በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሄዱ:: በውይይቱ ላይ የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ የታክስ ወንጀል ምርመራ ውስብስብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት መስራት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ጊዜያት ሁለቱ ተቋማት ባከናወኗቸው የቅንጅት ሥራዎች ለውጦች እየታዩ ቢሆንም በቀጣይ የታክስ ጉዳዮችን በተመለከተ የሚወሰኑ የታክስ ሕግ ውሳኔዎች ላይ በትኩረት እና በመቀራረብ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች መኖራቸውንም አክለዋል፡፡ ሀገራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ኢኮኖሚን መምራት ይገባል ያሉት ወ/ሮ ዓይናለም ሚኒስቴር መ/ቤቱም ይህንን ታሳቢ ባደረግ መልኩ እየሰራ እንዳለም ገልጸዋል፡፡ የፍትህ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሀና አርአያስላሴ በበኩላቸው ሚኒስቴር መ/ቤቱ የፍትህ ሥርዓቱን ለማሳደግ ለዳኞች፣ ለአቃቢያን ሕግ እና ለሌሎች ለሚመለከታቸው የፍትህ አካላት የአቅም ግንባታ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም ይሄው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ (የገቢዎች ሚኒስቴር)