የተቋሙ አጠቃላይ ገጽታ
ቢሮው በቀድሞው በደ/ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግስት ክልል በፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሥር በመምሪያ ደረጃ ተደራጅቶ የነበረ ሲሆን፣ ከህዳር ወር 1994 ዓ/ም ጀምሮ ራሱን ችሎ በቢሮ ደረጃ እንዲዋቀር ተደርጓል። ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የክልሉ መንግሥት ለሚያካሄዳቸው የልማት ፕሮግራሞች እና የመደበኛ አገልግሎቶች አቅርቦት የሚያስፈልገውን የወጪ በጀት መሸፈኛ የሚውል ገቢ ቀጣይነት ባለው አኳኋን ለማሳደግ እንዲያስችለው በቦርድ የበላይ ጠባቂነት የሚተዳደር የታክስ አስተዳደር ባለሥልጣን በሚል ስያሜ እንደገና እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡
ተቋሙ ታክስ እና የማዘጋጃ ቤቶች ገቢን ማስተዳደር እንዲችል በወቅቱ የክልሉን አስፈፃሚ አካላት ስልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን የሚያስችለውን አዋጅ ቁጥር 127/2002 እና እንደገና በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 133/2003 መሠረት የገቢዎች ባለሥልጣን በሚል ስያሜ ተቋቁሟል፡፡ ቢሮው ቀደም ሲል በነባሩ ክልል በተካሄደው የመሠረታዊ ሥራ ሂደት ለውጥ ጥናት የአገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሁም በተገልጋዩ ዘንድ አመኔታን ለማረጋገጥ እንዲቻል አደረጃጀቱ እስከ ክፍለ-ከተማ/ቀበሌ ድረስ እንዲዋቀር ተደርጓል፡፡ እንዲሁም ቀጥሎ በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 143/2004 ተቋሙ የታክስ ወንጀሎችን የመመርመር፣ የመክሰስ እና የማስወሰን ስልጣን ጭምር ተሰጥቶት ተቋሙ ትልቅ እምርታዊ ውጤት እያስመዘገበ ነበር፡፡
ተቋሙ በልዩ ሁኔታ የሰው ኃይል አደረጃጀት ያለው ከመሆኑም በላይ በህግ የተሰጠውን ሥልጣን፣ ኃላፊነትና ተግባር በብቃት እንዲወጣ የተሟላ ድርጅታዊ አቋም፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ የሚታገዝ፣ ቀልጣፋ የአሠራር ሥርዓት እንዲኖረው ለማስቻልና በክልሉ ኢኮኖሚ ውስጥ ካለው ሚና አንፃር የተለየ ትኩረት የሚሻ በመሆኑ ብቃት ያላቸውንና የተገልጋዩን ሕዝብ ፍላጎት ለማርካት የሚችሉ ባለሙያዎችን በመሳብና አይተከ ዕውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች ተቋሙ ላይ ለማቆየት የሚያስችል ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግ የተቋሙ የአሠራርና የሠራተኞች አስተዳደር ደንብ ቁጥር 94/2004 ወጥቶ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል።
ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት በቀድሞ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ራሱን ሪፎርም/ሪብራንድ/Rebrand/ አድርጎ ክልላዊ አደረጃጀት እንደራጅ ከተደረገ በኋላም በአገራችን እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ውጤታማ፣ ዘላቂና ተቋማዊ ለማድረግ እንዲሁም ከህብረተሰቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ተገቢና የተሟላ ምላሽ ለመስጠት የክልሉ መንግሥት ለሚያካሄዳቸው የልማት ኘሮግራሞች የሚያስፈልገውን የወጪ በጀት ለመሸፈን የሚውል ገቢ ቀጣይነት ባለው አግባብ መሰብሰብ እንዲቻልና ቢሮው በህግ የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዲያስችለው ዘመናዊ አሰራርና አደረጃጀት በመከተል ኃላፊነቱን መወጣት የሚጠበቅበት በመሆኑ የክልሉን አስፈፃሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 199/2015 መሠረት የገቢዎች ቢሮ በሚል ስያሜ የተቋቋመ ሲሆን በስሩ 7 የዞን መምሪያዎች፣ 3 ልዩ ወረዳዎች፣ 50 ወረዳዎች፣ 29 ከተማ አስተዳደሮች በጽ/ቤት ደረጃ እና 20 ታክስ ማዕከላት በድምሩ 109 መዋቅሮች በመያዝ በአዲስ መልክ የክልል ማዕከሉ መቀመጫ ቡታጅራ ከተማ በማድረግ እንድደራጅ ተደርጓል፡፡