Skip to main content
cerbornews4

የሀላባ ቁሊቶ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት ከሆቴል ባለቤቶች ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ። መጋቢት 23/2018 ዓ.ም የሀላባ ቁሊቶ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት በከተማዋ ከሚገኙ የሆቴል ባለቤቶች ጋር በታክስ ህጎች አተገባበር ዙሪያ ውጤታማ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የገቢዎች ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አብዲልቃድር ኢማም ሎላሶ ባስተላለፉት መልዕክት የሆቴል ዘርፍ ለከተማዋ ዕድገት ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ አገልግሎት አሰጣጥን ለህብረተሰቡ ምቹና ቀልጣፋ ማድረግና በሁሉም ሆቴሎች የታክስ ህጎችን ማክበር እና የደረሰኝ አሰጣጥ ስርዓትን በአግባቡ መተግበር እንደሚገባ ጠቁመዋል። 

ሆቴል ቤቶች ወርሃዊ የሪፖርት አቀራረብ እና የሂሳብ መዝገብ አያያዝን ሥርዓት ባለው መልኩ እንዲመሩ በማድረግ በታክስ መስሪያ ቤቱ እና በግብር ከፋዩ መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከርና የአፈጻጸም ችግሮችን በመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋገጠዋል። የሆቴል ዘርፍ ለከተማዋ የገቢ ምንጭ ብቻ ሳይሆን የከተማዋን ገጽታ ለጎብኚዎችና ለባለሀብቶች የሚያስተዋውቅ ዋነኛ ዘርፍ በመሆኑ የከተማዋ ዕድገት ከሆቴሎች አገልግሎት ጥራት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው በመገንዘብ ባለሀብቶች አገልግሎታቸውን ዘመናዊና ቀልጣፋ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። 

ትክክለኛና ወቅታዊ የሆነ የሂሳብ መዝገብ እንዲይዙ፣ ወርሃዊ የገቢ ሪፖርቶችን ያለ መዘግየት እንዲያቀርቡ እና በተለይም የደረሰኝ አሰጣጥ ስርዓትን በጥብቅ እንዲተገብሩ አሳስበዋል። በመድረኩ ላይ የተቋሙ የስራ ሂደት አስተባባሪዎች በአፈጻጸም ወቅት እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ከሆቴል ባለቤቶች ጋር በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል። በመጨረሻም አቶ አብዲልቃድር ከተማዋን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ግብርን በታማኝነት መክፈል የዜግነት ግዴታ መሆኑን ጠቅሰው ሆቴሎች የሚታዩባቸውን የአገልግሎት ውስንነቶች በማረም ለከተማዋ ብቁ የሆነ አገልግሎት እንዲሰጡና ለህግ ተገዢ በመሆን የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። የሀላባ ቁሊቶ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት