Skip to main content

የቢሮ ኃላፊ መልዕክት

መንግስት የሀገራችንን ብልጽግና በማረጋገጥ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ከምንጊዜውም በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ ሰንቆ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ዕድገት ፍኖት እና የፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ በመሆን ለአሥር ዓመታት የሚዘልቅ መሪ ዕቅድ በማዘጋጀት ላለፉት አራት ዓመታት ወደ ታለመው ከፍታ ለመድረስ በጥብቅ ዲስፕሊን እየሰራ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ገቢዎች ቢሮም በአገራዊና ክልላዊ የብልጽግና ዕቅድ ማዕቀፍ ውስጥ የሚፈጸም የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ሂደት በመግባት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የሚሄድ ውጤት በማስመዝገብ ላይ ይገኛል። 

በቀጣይም የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን በመፍታት በክልላችን ያሉንን የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ፀጋዎችን፣ የቱሪዝም መስህቦች፣ ምቹ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና የታታሪ ህዝቦች ባህልና ዕሴቶች በመጠቀም አዳጊ የሆኑ ፍላጎቶችን የማሟላት ሀላፊነቱን መወጣት እንዲችል ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስ ሀብት ማሰባሰብ ይጠይቃል፡፡ 

ዜጎች እንደሀገር ባሉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የመሳተፍና ተጠቃሚ የመሆን ህገ መንግስታዊ መብት እንዳለቸው ይታወቃል። በመረጡት የሥራ ዘርፍ በመሰማራት ከሚያገኙት ገቢ ላይም እንደገቢ መጠናቸው ግብረ የመክፈል ግዴታም ተጥሎባቸዋል። 

መንግስት ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ ያደረገው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የግሉን ዘርፍ የሚያበረታታ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሰፋፊ የሥራ መስኮች በመፈጠራቸው የዜጎች በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ መሆን የሚችሉባቸው በርካታ ዕድሎች ተፈጥረዋል፤ በዚህም ሂደት እንደሀገር ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል። 

በሀገሪቱ የመጣውን የሥርዓት ለውጥ ተከትሎም ተግባራዊ የተደረገው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ እያጋጠሙ ለነበሩ ችግሮች መሰረታዊ መፍትሄ እየሰጠ በመምጣቱም ምርትና ምርታማነት በስፋት እንዲጨምር ከማድረግ ባሻገር የነበረውን ኢኮኖሚያዊ እድገት በተሻለ ሁኔታ በማስቀጠል የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የምስራቅ አፍሪካ ትልቁ ኢኮኖሚ እንዲሆን እያስቻለ ይገኛል። 

መንግስት ግብር በመሰብሰብ ህገ-መንግስታዊ ሃላፊነቱን መሰረት በማድረግ የግብር ሥርዓቱ የሚመራባቸውን ህጎች በማውጣት እና የአሰራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ግብር በመሰብሰብ ለዜጎች የጋራ አገልግሎት ለሚሰጡ የመሰረተልማት ግንባታዎችና ለሌሎች መንግስታዊ አገልግሎቶች ማስፈፀሚያነት እንደሚያውል ይታወቃል። 

የክልሉ ገቢዎች ቢሮም በክልሉ ከሚከናወኑ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ተገቢውን ግብር በመሰብሰብ በመንግስት ለሚያዙ እና በክልሉ ለሚከናወኑ የልማት ዕቅዶች ማስፈፀሚያነት የሚያስፈልገውን የወጪ ሽፋን ለማሳደግ በርካታ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል። ቢሮው ተልዕኮውን በተገቢው ለመወጣትም ተቋማዊ የማስፈፀም አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ የአደረጃጀትና የአሰራር ስርዓቶች እና የህግ ማዕቀፎች ላይ ተከታታይ የማሻሻያ ስራዎችን ሰርቷል። በተለያዩ የንግድ መስኮች የተሰማሩ ዜጎች የግብር ስርዓቱን ለማስተዳደር የወጡ ህጎችንና የአሰራር ስርዓቶችን በማወቅና የህጉ ተገዥ በመሆን ባገኙት የገቢ መጠን ልክ ግብረ የመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን በፈቃደኝነትና በታማኝነት እንዲወጡ እና በተሰማሩባቸው የንግድ ስራዎች ውጤኣታማ በመሆኑ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ የተለያዩ የማስተማሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም በህጎችና አሰራር ስርዓቶች ላይ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። 

በግብር ህጎች ላይ የተሟላ ግንዛቤ ያለው ግብር ከፋይ ለመፍጠር ከሚከናወኑ የአስተምህሮት ስራዎች ጎን ለጎን ሆን ተብሎ የሚፈፀሙ የታክስ ስወራና ማጭበርብርን ለመከላከል የሚያስችሉ የህግ ማስከበር እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ።በቀጣይም ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሃብት መሰብሰብ ያለበትን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ ክልላዊ የወጪ ሽፋንን በማሳደግ የልማት ግቦችን ለማሳካት ሊከናወኑ የሚገባቸው በርካታ ተግባራት ያሉ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይም ከህግ ተገዥነት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ የታክስ ስወራና ማጭበርበር ወንጀሎችን ለመከላከል ግብር ከፋዮችን በስጋት መስፈርት የመለየት እና ተገቢውን መስተንግዶ ተግባራዊ የማድረጉ ተግባር ትኩረት ተሰጥቶት የሚተገበር ይሆናል። 

ከታክስ ደረሰኞች አጠቃቀም ጋር ተያይዞ በርካታ የታክስ ስወራና ማጭበርበር ወንጀሎችን ለመከላከል የተለያዩ አደረጃጀቶችን ተጠቅሞ በማስተማር እና የተቋሙ አጋር በማድረግ ሸማቹ የህብረተሰብ ክፍል ላይ ትኩረት ያደረጉ ተከታታይ ስራዎች ይሰራሉ። 

በተቋሙ በየደረጃው በሚገኙ ባለሙያዎች የሚታዩ የሥነ-ምግባር ጉድለት መነሻነት ሥር እየሰደደ የመጣውን ሌብነትና ብልሹ አሰራር ተገልጋዩን የህብረተሰብ ክፍል ከማማረር። የመንግስትን ግብር የግለሰቦች መጠቀሚያ ከማድረግ ባለፈ እንደተቋም የተሰጠንን መንግስታዊ ተልዕኮ በብቃት እንዳንወጣ ተግዳሮት እየሆነ በመምጣቱ ችግሩን ከመሰረቱ ለማስተካከል የሚያስችሉ ጠንከር ያሉ የእርምት እርምጃዎች እና የሪፎርም ስራዎች ይተገበራሉ። 

ከህግና አሰራር ውጭ በሆነ መንግድ አላስፈላጊ ግንኙነቶችን በመፍጠር የሚከናወኑ ብልሹ አሰራሮች ለመቀነስ እና የግብር አሰባሰብ ሂደቱን ለማዘመን በ2016 በደረጃ “ሐ” ግብር መክፈያ ወቅት በሙከራ የተጀመረውን ግብርን በቴሌ ብር እንዲከፈል በማድረግ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት አጠናክሮ በማስቀጠል፥ በቀጣይ E-tax እና E-filing ተግባራዊነት ላይ የተለየ ትኩረት በመስጠት የሚሰራ ይሆናል። 

በመሆኑም በየደረጃው የሚገኙ የተቋሙ አመራርና ባለሙያዎች በዋናነት የተጠቀሱትን ተግባራት ጨምሮ ሌሎችም ለገቢ አሰባሰብ ስርዓቱ ውጤታማነት ወሳኝ ድርሻ ያላቸው ተግባራትን በመፈፀም ለአጠቃላይ ተቋማዊ ተልዕኮ ስኬት ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ጥረትና ርብርብ ማድረግ ያለባቸው መሆኑን እና መላው የክልላችን ማህበረሰብም በግብይት ወቅት ተገቢውን ደረሰኝ በመውሰድ እና በታክስ/ግብር ማጭበርበር ድርጊትን በአስተሳሰብና በተግባር እንዲያነዉረዉ በማድረግ የክልላችን ብሎም የሃገራችን ልማት እንዳይደናቀፍ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪዬን አቀርባለሁ፤ አመሰግናለሁ።